የኔታ ቤት | ባህል | DW | 12.11.2020
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ባህል

የኔታ ቤት

በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ለልጆች አስተማሪ እና አዝናኝ ዝግጅቶችን በማቅረቡ የሚታወቀዉ እና ዋና መቀመጫዉን ቤልጂየም ያደረገዉ የኔታ ቤት ኮሮና ወረርሽኝ በዓለም መሰራጨት እንደጀመረ 75 ሺህ የሕክምና አፍና አፍንጫ መሸፈኛ ለኢትዮጵያ ድጋፍ በማድረጉ የኢትዮጵያዋ የጤና ሚኒስቴር ዶ/ር ሊያ ታደሰ ምስጋና አቅርበዋል።  

አውዲዮውን ያዳምጡ። 14:22

የቲቪ አዘጋጆች ድጋፍን ይሻሉ

በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ለልጆች አስተማሪ እና አዝናኝ ዝግጅቶችን በማቅረቡ የሚታወቀዉ እና ዋና መቀመጫዉን ቤልጂየም ያደረገዉ የኔታ ቤት ኮሮና ወረርሽኝ በዓለም መሰራጨት እንደጀመረ 75 ሺህ የሕክምና አፍና አፍንጫ መሸፈኛ ለኢትዮጵያ ድጋፍ በማድረጉ የኢትዮጵያዋ የጤና ሚኒስቴር ዶ/ር ሊያ ታደሰ ምስጋና አቅርበዋል።

የኔታ ቤት በቴሌቭዥን ለኢትዮጵያዉያን ሕጻናት ዝግጅትን የሚያቀርብ ሲሆን ኢትዮጵያ የኮቪድ ወረርሽን ለመከላከል በምታደርገዉ ጥረት የበኩሉን ድጋፍ ለማድረግ ቤልጂየም ዉስጥ ባገኘዉ እገዛ ነዉ 75 ሺህ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብሎችን ለማበርከት የበቃዉ። የኔታ ቤት የተሰኘዉ ለሕጻናት የሚቀርበዉ ዝግጅት በአብዛኛዉ አዉሮጳ ዉስጥ የሚቀናበር እና በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን በመደበኛነት ቅዳሜ እና እሁድ የሚተላለፍ ነዉ።

የሦስት ልጆች አባት እንደሆኑ የነገሩትን የፕሮግራሙ ዋና አዘጋጅ አቶ ዮሃንስ ዘርፉ እንደሚሉት ይህን ለሕጻናት የሚሆን ፕሮግራም ለማቀናበር እና ለኢትዮጵያ ሕጻናት በቴሌቭዥን እንዲተላለፍ ለማድረግ የወጠኑት ፤ የኢትዮጵያ ሕጻናት ባይታወር እንዳይሆኑ ፤ በማኅበረሰቡ ዉስጥም የበኩላቸዉን አስተዋጽ ማድረግ እንዲችሉ እና አዕምሮአቸዉን እንዲያሰፊ ነዉ። የኔታ ቤት የተሰኘዉ በቴሌቭዥን የሕጻናት ፕሮግራም ላይ ዮዮ የተባለዉ ታዋቂዉ ገፀ ባሕሪ በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ፕሮግራሙን በሚከታተሉ ሰዎች ዘንድ እዉቅናን ያገኘ መሆኑን አቶ ዮሃንስ ነግረዉናል። ይህን ዝግጅት ለሕጻናት ለማቅረብ ሃ ብለዉ የጀመሩት ግን በቴሌቭዥን ለማሰራጨት ሳይሆን በዉጭ የሚኑሩ ኢትዮጵያዉያን ሕጻናት ባህላቸዉን እንዲያዉቁ ሃገራቸዉን እንዲተዋወቁ ሲሉ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በማሰራጨት ነበር።

የኔታ ቤት ዘወትር ቅዳሜና እሁድ የሚቀርበዉ የሕጻናት ዝግጅት ከሰኞ እስከ አርብም ባሉት ቀናት ደግሞ ይታያል። በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ለእይታ የሚቀርበዉ እና ምዕራቡ ዓለም የሚቀረፀዉ ይህ የ 10 እና 15 ደቂቃዎች የሕጻናት ፕሮግራም በአዉሮጳ የኑሮ ሩጫ ተግዳሮቱ ምን ያህል ይሆን? አቶ ዮሃንስ ቀላል እንዳልሆነ ይናገራሉ ።

ቤልጂየም አንትቪርፍ ከተማ ነዋሪ የሆኑት የኔታ ቤት ዋና አዘጋጅ አቶ ዮሃንስ ዘርፉ፤ ይኽን ለሕጻናት የሚሆን የቴሌቭዥን ፕሮግራም የሚያዘጋጁት ከአንድ ጓደኛቸዉ ጋር ሆነዉ ነዉ። ምን አይነት የገቢ ምንጭም ሆነ ድጋፍ የላቸዉም። በአዲስ አበባ ቀረጻ ሲኖርም አንድ የሚረዳቸዉ ወዳጃቸዉ ይረዳቸዋል። ይሁንና በመለጠቅ በአዲስ አበባ ቢሮ ለመክፈት ፍላጎት እንዳላቸዉ ተናግረዋል። ዋናዉ የሚያሳስባቸዉ ነገርም ፤ ኢትዮጵያ ዉስጥ ለሕጻናት እና ለልጆች የሚሰጠዉ ግምት እጅግ ዝቅተኛ መሆኑ ነዉ።

የኔታ ቤት ቴሌቭዝን ዝግጅት የሚሰጠዉ አስተዋጽኦ ይበል የሚሰኝ ነዉ ። የኔታን በሃሳብም ሆነ በአቅም ለመደገፍ የምትሹ፤ ለዝግጅት ክፍላችን ብትጽፉ መልክቱን እናስተላልፋለን አልያም በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ የኔታ ቤት ብላችሁ ብትፈልጉ ይገኛል።

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን ይከታተሉ!

አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic