የኮሮና ክትባት ፍትሐዊ ሥርጭት  | ኤኮኖሚ | DW | 25.11.2020
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኤኮኖሚ

የኮሮና ክትባት ፍትሐዊ ሥርጭት 

ዓለም የኮሮና ወረርሽኝ ከበረታባቸው ዐሥር ፈታኝ ወራት በኋላ የተስፋ ጭላንጭል ማየት ጀምሯል። ሦስት ክትባቶች የኮሮና ሕመምን በመከላከል ረገድ ስኬታማ ውጤት እንዳሳዩ ተገልጿል። የበለጸጉት አገሮች ቅድሚያ ሥምምነት እየፈጸሙ ክትባት ለመግዛት ሲዋዋሉ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች ዓለም አቀፍ ሥምምነቶችን እየተጠባበቁ ነው

አውዲዮውን ያዳምጡ። 08:54

የኮሮና ክትባት ፍትሐዊ ሥርጭት

ፋይዘር የተባለው የአሜሪካ ኩባንያ እና የጀርመን አጋሩ ባዮንቴክ ለኮሮና መከላከያ ያዘጋጁት ክትባት ሥራ ላይ እንዲውል ከአሜሪካ የምግብ እና የመድሐኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን (FDA) ፈቃድ መጠየቃቸውን ባለፈው ሳምንት አስታውቀዋል። ፋይዘር የተባለው የአሜሪካ ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አልበርት ቦርላ ይኸው ክትባት ለአስቸኳይ ግልጋሎት ሥራ ላይ እንዲውል ፈቃድ መጠየቃቸውን አረጋግጠዋል። የአሜሪካው ግዙፍ የመድሐኒት አምራች ፋይዘር እና ባዮንቴክ የተባለው የጀርመን አጋር ኩባንያ ኮሮናን ለመከላከል ያዘጋጁት ክትባት 95 በመቶ ስኬታማ መሆኑን አስታውቀው ነበር።

ሞዴርና በተባለ ሌላ የአሜሪካ ኩባንያ በተናጠል እንዲሁም የስዊትዘርላንዱ አስትራዜኔካ ከብሪታኒያው ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የሚሞክሯቸው ክትባቶች ስኬታማነት በየተቋማቱ ተገልጿል። በተለይ በምዕራባውያን ኩባንያዎች የተዘጋጁት ሶስት ክትባቶች እስከ ማክሰኞ ሕዳር 15 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ ብቻ በአሜሪካ ጆን ኾፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ መረጃ መሰረት ከ1.4 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ለገደለው እና ከ59 ሚሊዮን 462 ሺሕ በላይ ሰዎች ለያዘው የኮሮና ወረርሽኝ መፍትሔ ይሆናል የሚለው ተስፋ ካለፉት ሳምንታት ተጠናክሯል። የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድኃኖም የክትባቶቹ ዜና መልካም ቢሆንም የሥርጭት ጉዳይ እንደሚያሳስብ ባለፈው ሰኞ ተናግረዋል።

ዶክተር ቴድሮስ አድኃኖም "በክትባት ሙከራዎች በተሰማው አዎንታዊ ዜና በዚህ ረዥም እና ጭለማ የበረታበት ዋሻ መጨረሻ የሚታየው ብርሀን ጠንካራ እየሆነ ነው። ክትባቶች ከሌሎች ከተሞከሩ እና ከተፈተሹ የማሕበረሰብ ጤና እርምጃዎች ጋር ወረርሽኙን ለማቆም እገዛ እንደሚያደርጉ አሁን ተጨባጭ ተስፋ አለ። ሳይንሳዊው ስኬት በፍጹም የሚናቅ አይደለም። በታሪክ ምንም አይነት ክትባት በዚህ ፍጥነት ተዘጋጅቶ አያውቅም። የሳይንሱ ማሕበረሰብ ለክትባት ዝግጅት አዲስ ልክ አስቀምጠዋል። አሁን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለአቅርቦት አዲስ መንገድ መቀየስ አለበት። በክትባት ዝግጅት የታየው ጥድፊያ ሥርጭቱን በፍትሐዊነት ለማዳረስም ሊኖር ይገባል። እያንዳንዱ መንግሥት ዜጎቹን ከወረርሽኙ ለመጠበቅ የሚችለውን ሁሉ ያደርጋል። ነገር ግን ደሐ እና ተጋላጭ የሆኑ ሕዝቦች ክትባቱን ለማግኘት በሚደረገው ግፊያ የመረጋገጥ ሥጋት ተጋርጦባቸዋል።" ብለዋል።

Tedros Adhanom Ghebreyesus, Direktor WHO

የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድኃኖም

ይኸ የዶክተር ቴድሮስ አድኃኖም ሥጋት በተጨባጭ በዓለም ገበያ ከሚታየው እውነታ የተስማማ ነው። የናጠጡት አገሮች ክትባቶቹ ፍቱንነታቸው ተረጋግጦ ሥራ ላይ እንዲውሉ ገና ባይፈቀድላቸውም በርከት ያለውን አስቀድመው ለመግዛት እየተስማሙ በዓለም አቀፍ ሥርጭቱ ፍትሐዊነት እንዳይኖር አድርገዋል የሚል ሥጋት በበርካታ ባለሞያዎች ዘንድ አይሏል።
የኮሮና ክትባቶችን በመላው ዓለም በፍትሐዊነት ለማዳረስ ስምምነቶች ቢኖሩም በደሐ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገሮች የሚኖሩ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በሚቀጥለው አንድ ዓመት ግፋ ሲልም እስከ ጎርጎሮሳዊው 2024 ዓ.ም. ሳይከተቡ ሊቀሩ እንደሚችሉ የአሜሪካው ዱክ ዩኒቨርሲቲ ያከናወነው አንድ ጥናት ያሳያል። ለዚህ አንዱ ምክንያት የናጠጡት አገሮች ያላቸው የፈረጠመ የገንዘብ አቅም ነው። የክትባቶቹ ፍቱንነት ተረጋግጦ ሥራ ላይ እንዲውሉ ቢፈቀድ እንኳ ዓለም አምርቶ ለገበያ የማቅረብ አቅሙ ውስን ነው። እስካለፈው ጥቅምት ወር ብቻ ከፍተኛ እና መካከለኛ ገቢ ያላቸው አገሮች ሊመረቱ የሚችሉ ክትባቶችን አስቀድመው ለራሳቸው ለመግዛት ሥምምነት ሲፈጽሙ ለደሐዎቹ ያስቀሩት ውስን መሆኑ የሥጋት ምንጭ ነው።

የዱክ ዩኒቨርሲቲ ጥናት እንደሚያሳየው በተለይ የናጠጡት አገሮች በሰዎች ላይ የሚደረገው ሙከራ ሳይጠናቀቅ ከአምስት ቢሊዮን በላይ ክትባቶች አስቀድመው ገዝተዋል፤ አሊያም ለመግዛት በድርድር ላይ ናቸው። ሕንድ 1.6 ቢሊዮን፣ ብራዚል 200 ሚሊዮን ክትባቶች የመግዛት ሥምምነት ከአምራች ኩባንያዎች ፈጽመዋል። ለደሐ አገሮች የቀረው ጥቂት ከመሆኑ ባሻገር የክትባቶቹ ፍቱንነት ገና በይፋ ባለመረጋገጡ የናጠጡት ከአንድ በላይ እጩ ክትባቶችን ለመግዛት ውል እየፈጸሙ የፍትሐዊ ክፍፍልን ነገር ጥያቄ ውስጥ ከተውታል።

ተስፋ የተጣለበት ኮቫክስ እና ፈተናው

የዱክ ዩኒቨርሲቲ የጥናት ባለሙያዎች እንደሚሉት ኢትዮጵያ ከአጠቃላይ የሕዝብ ቁጥሯ 20 በመቶውን ለመከተብ የሚያስችል መጠን ኮቫክስ በተባለው ዓለም አቀፍ ጥምረት በኩል ልታገኝ ትችላለች። በዚሁ ጥናት መሠረት ኢትዮጵያ ተጨማሪ ክትባት በእጇ ለማስገባት የምትችልበት መንገድ ግን የላትም። ኮቫክስ ክትባቶችን በፍትሐዊነት ለማሰራጨት በአገሮች መካከል የተፈረመ ሥምምነት ነው። የሥምምነቱ ፈራሚዎች ሥራ ላይ ሊውል የሚችል የኮሮና መከላከያ ክትባትን በፍትሐዊነት ለመከፋፈል ውል ቢኖራቸውም እንደ ብሪታኒያ፣ የአውሮፓ ኅብረት እና ካናዳ ያሉ አገሮች ከአምራቾች የጎንዮሽ ውል እየፈረሙ የዕቅዱን ስኬታማነት ጥያቄ ውስጥ እንደጣሉት የዱክ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ገልጸዋል። ለዚህ ኹነኛ ማሳያ የአውሮፓ ኅብረት ክትባቶች ቀድሞ ለመግዛት የገባቸው ስምምነቶች ናቸው።
በዝግጅት ላይ የሚገኙ ክትባቶችን አስቀድሞ ለማግኘት የተለያዩ ስምምነቶች ስትፈጽም የቆየችው አውሮፓ ትናንት ማክሰኞ ሞዴርና ከተባለው ኩባንያ ሌላ ውል ገብታለች። ይኸኛው ውል ከአሜሪካው የመድሐኒት አምራች 160 ሚሊዮን ክትባቶች ለመግዛት የሚያስችል እንደሆነ የአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ፎን ደር ላየን ተናግረዋል።
ኡርሱላ ፎን ደር ላየን "ይኸ የኮሮና ክትባትን ለመግዛት የተዋዋልንው ስድስተኛ ስምምነት ነው። አንድ ሌላ ለመጨመር እየሰራን ነው። በዓለም የተሻለ የኮሮና ክትባት ማደራጀታችን ለአውሮፓውያን በሙከራ ላይ ከሚገኙት ክትባቶች ተስፋ ሰጪዎቹን እንዲያገኙ ዕድል ይሰጣል።" ሲሉ ተናግረዋል።

ኡርሱላ ፎንደር ላየን ቅድሚያ ለአውሮፓ መሠጠቱን ቢናገሩም የተቀረውን ዓለም አልዘነጋንም ብለዋል። ፕሬዝዳንቷ እንዳሉት ኅብረቱ በኮቫክስ አማካኝነት የኮሮና ክትባት በፍትሐዊ መንገድ እንዲሰራጭ የገንዘብ መዋጮ እያደረገ ነው። "አውሮፓውያን ደሕንነቱ የተረጋገጠ ክትባት እንዲያገኙ ማድረግ አንድ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው። ሌላው አንገብጋቢ ጉዳይ በየትኛውም የዓለም ክፍል የሚገኝ ማንኛውም ሰው ክትባቱን የማግኘት ዕድል እንዳለው ማረጋገጥ ነው። የክትባቶቹ ዋጋም ሆነ ክፍፍሉ ፍትሐዊ መሆን አለበት። ለዚህም ነው በመላው ዓለም ለኮሮና ምርመራ፣ ሕክምና እና ክትባት ካለፈው ግንቦት ጀምሮ 16 ቢሊዮን ዩሮ ለመስጠት ቃል የገባንው። ከፍተኛ ገቢ ባላቸው አገራት በሚሰጡት የገንዘብ ድጋፍ ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው አገራት አሁንና ወደፊት የሚመረቱ ክትባቶችን ማግኘታቸውን ለማረጋገጥ ለተቋቋመው የኮቫክስ ሥምምነት አውሮፓ 800 ሚሊዮን ዶላር አዋጥተናል።" ሲሉ ተደምጠዋል።

በሳምንቱ መገባደጃ በተካሔደው የቡድን 20 አባል አገራት የኢንተርኔት ስብሰባ ዋንኛ አጀንዳ ከነበሩ ጉዳዮች መካከል ይኸው የኮሮና ክትባት ሥርጭት ጉዳይ እና ወረርሽኙ ያስከተለው ዓለም አቀፍ ምጣኔ ሐብታዊ ቀውስ ይገኝበታል። በስብሰባው የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ያደረጉት ንግግር በቡድን 20 አባል አገራት ዘንድ የኮሮና ክትባት ሥርጭት ፍትሐዊ እንዲሆን መግባባት ለመኖሩ ጥቆማ የሰጠ ነበር።
ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ "በቡድን 20 አባል አገራት ዘንድ ፍቱን የኮቪድ 19 ክትባት የማግኘት ዕድል በመላው ዓለም ፍትሐዊ እና ሚዛናዊ እንዲሆን መግባባት በመኖሩ ደስተኛ ነን" በማለት ተናግረዋል።

የኮሮና ክትባት ባለቤት ለመሆን በሚደረግ ሽቅድምድም መካከለኛ ገቢ ያላቸው አገሮች ከናጠጡት ትከሻ መጋፋት ባይሆንላቸውም የተለያዩ ዘዴዎችን እየተጠቀሙ ነው። በአሜሪካዋ ኖርዝ ካሮላይና ግዛት የሚገኘው የዱክ ዩኒቨርሲቲ ጥናት እንደሚያሳየው ብራዚል እና ሕንድ በአገራቸው የሚገኙ ግዙፍ የክትባት ማምረቻዎችን እንደ መደራደሪያ ተጠቅመው ክትባቱን እጃቸው ለማስገባት የሚያስችል ሥምምነት ፈጽመዋል። ፔሩ በአንፃሩ ከዓለም አቀፉ የኮቫክስ ሥምምነት በተጨማሪ የኮሮና ክትባት ሙከራ በዜጎቿ ላይ መካሔዱን እንደ መደራደሪያ ተጠቅማለች።
ጋቪ የተባለው ዓለም አቀፍ የክትባት አቅርቦት ጥምረት ኢትዮጵያን ጨምሮ በግላቸው ተደራድረው መሸመት ለማይችሉ ለ92 አገሮች ክትባቶች ገዝቶ ለማሰራጨት 2 ቢሊዮን ዶላር ገደማ መሠብሰቡን አረጋግጧል። ይኹንና በሚቀጥለው የጎርጎሮሳዊው 2021 ዓ.ም. አምስት ቢሊዮን ዶላር ያስፈልገዋል።

Deutschland Berlin | Angela Merkel Pressekonferenz nach EU-Videogipfel

መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል

በጋቪ በኩል ክትባቶችን በመግዛት እና በማከፋፈል በአገሮች መካከል ፍትሐዊ የሥርጭት ሥርዓት ለመዘርጋት የታቀደበትን የኮቫክስ ሥምምነት በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ክትባቶች ከአምራቾች ለመግዛት ውል ፈጽሟል። ለጀርመኗ መራሒተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል በተለይ ለደሐ አገሮች ክትባት ለማቅረብ ምንም አለመደረጉ ያሳሰባቸው ይመስላል።
መራሒተ መንግሥት አንፌላ ሜርክል"ድርድሮቹ በትክክል መቼ እንደሚጀመሩ ለማወቅ ከጋቪ ጋር እንነጋገራለን። እስካሁን ምንም አለመጀመሩ አሳስቦኛል። ገንዘቡ አልቆ ከሆነ እናያለን። አንዳንድ ጊዜ ጀርመን ምንም ማድረግ አትችልም። ይሁንና ጀርመን ዓለም አቀፉን ጥምረት ብቻውን እንዲቆም አታደርግም። በዚህ ወቅት ግን ትክክለኛውን ነገር ማድረግ ያስፈልጋል። ገንዘብ ሰብስቦ በባንክ ማስቀመጥ ብቻውን በቂ አይደለም። በማደግ ላይ ለሚገኙት አገሮች የሆነ ነገር ሊደረግ ይገባል።" ብለዋል።

እሸቴ በቀለ
ማንተጋፍቶት ስለሺ


Audios and videos on the topic